የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ባወጣው አዲስ መመሪያ መሠረት፤ በሕንጻ ግንባታ ወቅት የአደጋ ጊዜ መውጫ አሳንሰር እና ሌሎች የግንባታ መስፈርቶችን በማያሟሉ ገንቢዎች ላይ የሚጣለው ከ3 እስከ 5 ሚሊየን ብር ቅጣት አሁን ላይ ወደ 60 ሚሊየን ብር ከፍ መደረጉ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ደሲሳ ለአሐዱ እንደገለጹት፤ ይህ የገንዘብ ቅጣት እንዲሻሻል የተደረገው መመሪያዎችን የማያሟሉ አካላትን ቁጥር ለመቀነስ እንዲሁም ሕንጻዎች በዲዛይንም ሆነ በግንባታ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲሰሩ ለማድረግ ነው።
“በከተማዋ በ2016 በተደረገ ዳሰሳ ከ52 ሺሕ 600 በላይ ሕንጻዎች ይገኛሉ” ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በእነዚህ ሕንጻዎች ላይ በየአራት ዓመቱ የሚደረገው ፍተሻ አሁን ወደ ሁለት ዓመት ዝቅ እንዲል መደረጉን ጨምረው ተናግረዋል፡፡
አሐዱም “በዚህ አዲስ አሠራር መሠረት ምን ያክል ገንቢዎች ተጠያቂ ተደረጉ?” ሲል ላነሳው ጥያቄ ቁጥራዊ መረጃዎችን ከመስጠት የተቆጠቡት አቶ ገዛኸኝ፤ ነገር ግን “ከሕንጻዎች የአደጋ ጊዜ መውጫ ብረቶች መስፈርት (ስታንዳርድ) ጋር በተያያዘ የሚወስነው የሕንጻው ከፍታና የሚይዘው ክብደት ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ይህ መስፈርት የሚሰራው ለአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ከ12 ሜትር እና ለመኖሪያ ቤቶች ከ20 ሜትር በላይ የሆኑ ሕንጻዎች ላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
አሐዱሬዲዮ
